የኢትዮጵያውያን  ፡ ሀገራዊ  ፡ ሥልጡንሕዝባዊ  ፡ አንድነት  ። Ethiopians' Citizen Democratic Union | Union Citoyenne Démocratique des Éthiopiens www.slttunhzb.net ገ_ዐዓ_20130101_ዐማርኛ ለ2013 ፡ ዓ.ም. ፡ የመልካም ፡ ምኞት ፡ መግለጫ ። ዐዲሱ ፡ ዓመት ፥ በዐዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት ፥ ለዐዲስ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ መንግሥት ፡ ያብቃን ! _______ ለንደን ፥ መስከረም ፡ 1 ፡ ቀን ፥ 2013 ፡ ዓ.ም. ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ፤ 2012 ፡ ዓ.ም. ፡ አንተና ፡ እግዚአብሔር ፡ ብቻ ፡ የምታውቁት ፥ ዓለም ፡ ሊያውቅልኽ ፡ ያልፈለገው ፡ የመከራና ፡ የጭቈና ፣ የግፍና ፡ የበደል ፣ የብዝበዛና ፡ የምዝበራ ፣ የቅሥፈትና ፡ የቀጠና ፣ የፍጅትና ፡ የዕልቂት ፣ የክዳትና ፡ የዕብለት ፣ የውርደትና ፡ የተግዳሮት ፡ ዓመት ፡ ኾኖብኽ ፡ ዐለፈ ። 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ የባሰ ፡ እንዳይኾን ፡ የሚያደርግልኽ ፥ ከእግዚአብሔርና ፡ ከራስኽ ፡ በቀር ፥ ማንም ፡ የለምና ፥ በምግባርኽ ፡ ዅሉ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ ተመቸው ፤ ራስኽም ፡ የባለሀገርነት ፡ መብትኽንና ፡ ግዴታኽን ፡ ዐውቀኽ ፥ የሚጠ፟በ፟ቅብኽን ፡ ግዴታ ፡ ዅሉ ፡ ለመወጣትና ፡ የሚጠየቀውን ፡ ዋጋ ፡ ዅሉ ፡ ለመክፈል ፥ አረንጓዴ ፡ ብጫ ፡ ቀይ ፡ አንድያ ፡ ሰንደቅ ፡ ዐላማኽን ፡ ይዘኽ ፥ ቈርጠኽ ፡ ተነሥ ! «በራ፟ቸውን ፡ ክፍት ፡ ትተው ፥ ሰውን ፡ "ሌባ" ፡ ይላሉ ።» የምታውቀው ፡ ብሂል ፡ ነው ። እግዚእናኽን ፣ ባለሀገርነትኽን ፣ ባለቤትነትኽን ፡ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ባለማስከበርኽ ፥ እንሆ ፥ ከረዥም ፡ ዘመን ፡ አንሥቶ ፡ ሀገርኽ ፡ በውንብድና ፡ ኀይሎች ፡ ስትቈራረስና ፡ ስትበዘበዝ ፥ አንተም ፡ ስትጨቈንና ፡ ስትባረር ፡ ትኖራላችኹ ። ለሀገርኽ ፣ ለእግዚእናኽና ፡ ለነጻነትኽ ፡ መከበር ፡ በተናጠል ፡ የሚታገሉልኽ ፡ ልጆችኽ ፡ በግፍ ፡ ተገድለዋል ፤ የተሰደዱትም ፡ ተሰደ፟ው ፥ የተረፉት ፡ ጧት ፡ ማታ ፡ እንደ ፡ ጥጃ ፡ ሲፈ፟ቱ፟ና ፡ ሲታሰሩ ፡ እንሆ ፡ ታያቸዋለኽ ። እስከ ፡ መቼ ፧ «የሞኝ ፡ ለቅሶ ፥ መልሶ ፡ መልሶ» ፡ እንዲሉ ፥ በደልኽንና ፡ ብሶትኽን ፡ እየነገሩና ፡ እየዘገቡ ፡ የሚቈዝሙ ፡ አልጠፉም ። ይህ ፡ ግን ፡ መፍትሔ ፡ አልኾነልኽም ። እንዲያውም ፡ ጨቋኞችኽን ፡ የልብ ፡ ልብ ፡ በቃቸው ፤ አፍ ፡ አውጥተው ፡ «ምን ፡ እንዳታመጣ ፧» ፡ ይሉኽ ፡ ዠምረዋል ። እስከ ፡ መቼ ፧ ታጋሽነት ፡ የታላቅ ፡ ሕዝብ ፡ ዅሉ ፡ መገ፟ለጫ ፡ የኾነውን ፡ ያኽል ፥ ትግሥት ፡ ደግሞ ፡ ወቅቱን ፡ ለጠበቀ ፡ ድርጊያ ፡ የሚውል ፡ ታላቅ ፡ ስልት ፡ ነው ። 2013 ፡ ዓ.ም. ፡ የድል ፡ በዓል ፡ 80ኛ ፡ ዓመት ፡ መታሰቢያም ፡ ነውና ፥ ፋሺስታዊ ፡ ውንብድናን ፡ በማስወገድ ፥ ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ አስከብረኽ ፥ በዐዲስ ፡ ሀገራዊ ፡ ኪዳን ፥ ዐዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥትኽን ፡ በመሥራት ፥ ዐዲሱን ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ መንግሥትኽን ፡ የምትከውንበት ፡ የድርጊያና ፡ የድል ፡ ዓመት ፡ እንዲኾንልኽ ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ ውጥን ፡ አካልኽ ፡ የኾነው ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ ከልብ ፡ ይመኝልኻል ። ከመመኘትም ፡ ጋራ ፥ ለሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽ ፡ ለኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ በማበር ፥ መብትንና ፡ ተገቢነትን ፣ ግዘፍንና ፡ ችሎትን ፣ ምላትንና ፡ ብቃትን ፡ ሰጥተኸው ፥ ትግልኽን ፡ በገቢር ፡ የምታሳካበት ፡ ዓመት ፡ ይኾንልኽ ፡ ዘንድ ፥ የአንድነት ፡ ጥሪውን ፡ በሀገር ፡ ፍቅር ፡ ያስተላልፍልኻል፨ ትሑት ፡ አገልጋይኽ፦ ኢ.ሀ.ሥ.አ.