የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ። Ethiopians' Citizen Democratic Union | Union Citoyenne Démocratique des Éthiopiens የመርበቢያ ፡ አድራሻ ፤ www.slttunhzb.net የእ-ጦማር ፡ አድራሻ ፤ sh1@ttomar.net ________________________________ የኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ የትንሣኤ ፡ እና ፡ የድል ፡ በዓል ፡ መልካም ፡ ምኞት ፡ መልእክት ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፦ « ዳግማዊ ፡ ዐድዋ ! » _______ ለንደን  ፥ ሚያዝያ ፡ 5 ፡ ቀን ፡ 2018 ፡ ዓ.ም.  ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! ቀዳማዊው ፡ የዐድዋ ፡ ድል ፥ የካቲት ፡ 23 ፡ ቀን ፡ 1888 ፡ ዓ.ም. ፥ ከኢትዮጵያ ፡ እና ፡ ከአፍሪቃ ፡ ዐልፎ ፥ በመላ፟ ፡ ዓለም ፡ የሰው ፡ ልጆች ፡ እኩልነት ፡ እንዲውን ፡ እና ፡ የቅኝ-ግዛት ፡ ሥርዐት ፡ ከሥር ፡ ከመሠረቱ ፡ ተናግቶ ፥ ከስድሳ ፡ ዓመታት ፡ በዃላም ፡ ፈራርሶ ፡ እንዲቀበር ፡ ያደረገ ፥ በሥልጣን ፡ ተገቢነት ፡ እና ፡ በሥልጣኔ ፡ ላቂያ ፡ የተገኘ ፡ የኢትዮጵያ ፡ እና ፡ የሀገራዊ ፡ ሕዝቧ ፡ ዘለዓለማዊ ፡ ድል ፡ ነው ። ዛሬ ፥ የዐድዋን ፡ ድል ፡ በዓል ፡ 130ኛ ፡ ዓመት ፡ መታሰቢያ ፡ ስናከብር ፥ ኢትዮጵያ ፡ ዳግመኛ ፡ በምልክዮሽ ፡ መዳፍ ፡ ውስጥ ፡ ወድቃ ፥ እግዚእናዋን ፡ ዐጥታ ፥ በሥልጣን ፡ ጦርነት ፡ ውስጥ ፡ ተዘፍቃ ፥ በሞት ፡ ሽረት ፡ ትግል ፡ ውስጥ ፡ ትገኛለች ። የኢትዮጵያ ፡ ሀገራዊ ፡ ሕዝብ ፡ ዐምሐራ ፥ በፋኖ፟ነት ፡ ተደራጅቶ ፥ ከፍ ፡ ያለውን ፡ የሕይወት ፡ ዋጋ ፡ ሳይሣሣ ፡ እየከፈለ ፥ ሥልጡን ፡ ሀገሩን ፡ ኢትዮጵያን ፡ ሊታደጋት ፡ ተሰልፏል ። እፊቱ ፡ የገጠመው ፡ በእጅ-አዙር ፡ የሚዋጋ ፡ የሰንደቃዊ ፡ ምልክዮሽ ፡ (የ"ግሎባል ፡ ኢምፔሪያሊዝም") ፡ ኀይል ፡ ነው ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፥ ከጥንት ፡ ዠምሮ ፡ በሕጋዊ ፡ ሥልጣን ፡ የመመራት ፡ ሥርዐቱን ፡ እስካጣ ፡ ድረስ ፥ ለድል ፡ እንደማይበቃ ፡ ምልክዮሽ ፡ ስላረጋገጠ ፥ የኢትየጵያን ፡ ሕዝብ ፡ ከሕጋዊ ፡ አመራር ፡ ማራቅን ፡ ዋነኛው ፡ የጥቃት ፡ ስልቱ ፡ አድርጎታል ። ደግመው ፡ ደጋግመው ፡ የሚ፟ነ፟ሡ፟ት ፡ የትግል ፡ ቡድኖች ፡ ዅሉ ፥ ወይ ፡ በባዕድ ፡ "አይዲዮሎጂ" ፡ የሰከሩ ፡ ፍሬ-ቢሶች፣ ወይ ፡ በ"ክልል" ፡ የጠበቡ ፡ ስኡኖች ፡ እየኾኑ ፥ የዐድዋ ፡ ፍሬዎች ፡ ዅሉ ፡ አንድ ፡ ባንድ ፡ እየተበሉ ፥ ምልክዮሽ ፡ እና ፡ ግብር-ዐበሮቹ ፡ ምንም ፡ ሳይሠጉ ፥ እንሆ ፥ ለ50 ፡ ዓመታት ፡ ሀገር ፡ ኢትዮጵያን ፡ የማፈራረስ ፡ ርኩስ ፡ ግብራቸውን ፡ ቀጥለዋል ። ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፥ ይህን ፡ የጥፋት ፡ አካኼድ ፡ ጠቍሞ ፡ በማመልከት ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሕጋዊ ፡ አንድነታዊ ፡ ሥልጣኑን ፡ በፍጥነት ፡ እንዲያበጅ ፡ እና ፡ እንዲድን ፡ ኀምሳ ፡ ዓመታት ፡ ሙሉ ፡ መልእክቱን ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሲያስተላልፍ ፡ ቈይቷል ። በተፈለገው ፡ ፍጥነት ፡ አልተሰማም ፤ ማወራኛውም ፡ ቢኾን ፥ መልእክቱን ፡ ለመላ፟ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ለማድረስ ፡ አልተባበረውም ። ለሀገር ፡ ህልውና ፡ እስከ ፡ ኾነ ፡ ድረስ ፥ ለ50 ፡ ዓመታት ፡ ይቅርና ፥ ለ5000 ፡ ዓመታትም ፡ ሳይሰለቹ ፡ በወተወቱ ። ምልክዮሽ ፥ በጥፋት ፡ ዐቅዱ፦ "የኹለት ፡ ትውልድን ፡ ናላ ፡ በከፋፋይ ፡ ስብከት ፡ ከሰበ፟ክኹት ፡ ወዲያ ፥ የአንድነት ፡ ዐርበኝነት ፡ በኢትዮጵያ ፡ ምድር ፡ አይታሰብም !" ፡ ብሎ ፡ ነበር ። ዳሩ ፡ ግን ፥ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! ልጅኽ ፡ ፋኖ፟ ፡ የዐርበኝነቱን ፡ ፈር ፡ ተልሞልኻል ! ሥልጣኔኽን ፡ አንግበኽ ፥ ይህን ፡ የሰንደቃዊ ፡ ምልክዮሽን ፡ የጥፋት ፡ ዐቅድ ፡ ዳግመኛ ፡ ለማምከን ፡ ለዳግማዊ ፡ ዐድዋ ፡ ተነሣ ! ስት፟ነ፟ሣ፟ም ፥ እግዚአብሔር ፡ ይረዳኻል ፨ ትሑት ፡ አገልጋይኽ ፥ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ።