የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ። Ethiopians' Citizen Democratic Union | Union Citoyenne Démocratique des Éthiopiens የመርበቢያ ፡ አድራሻ ፤ www.slttunhzb.net የእ-ጦማር ፡ አድራሻ ፤ sh1@ttomar.net ________________________________ ገ_ት-ድበ_20170827_ዐማርኛ የኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ የትንሣኤ ፡ እና ፡ የድል ፡ በዓል ፡ መልካም ፡ ምኞት ፡ መልእክት ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፦ « ርትዕ ፡ እና ፡ መሥዋዕት ፥ የድል ፡ መሠረት ! » _______ ለንደን ፥ ሚያዝያ ፡ 27 ፡ ቀን ፡ 2017 ፡ ዓ.ም. ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! እንኳን ፡ ለጌታችን ፡ ለመድኀኒታችን ፡ ኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ የትንሣኤ ፡ በዓል ፡ እና ፡ ለሚያዝያ ፡ 27 ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሀገራዊ ፡ ድል ፡ በዓል ፡ በሰላም ፡ አደረሰኽ ፡ እያ፟ለ ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ ውጥ፟ን ፡ አካልኽ ፥ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ ( ኢ.ሀ.ሥ.አ. ) ፡ መልካም ፡ ምኞቱን ፡ በትሕትና ፡ ያቀርብልኻል። የትንሣኤ ፡ በዓልን ፡ እና ፡ የድል ፡ በዓል ፡ 84ኛ ፡ ዓመትን ፡ በምናከብርበት ፡ ሰሞን ፥ በዠግኖች ፡ ልጆችኽ ፡ የፋኖ፟ ፡ ንቅናቄ ፡ አባላት ፡ ተጋድሎ ፥ ዳግም ፡ የድል ፡ አድራጊነትን ፡ እና ፡ የሀገራዊ ፡ ድኅነትን ፡ መልእክት ፡ ከእየአግጣጫው ፡ እየሰማኽ ፥ የተስፋኽን ፡ ፍሬ ፡ ለማየት ፡ ትጠባበቃለኽ ። የጥቂቶቹ ፡ መሥዋዕት ፡ ሀገርን ፡ ያኽል ፡ ታላቅ ፡ እና ፡ ክቡር ፡ አለኝታን ፡ ስለ ፡ መታደጉ ፡ የሚያዝያ ፡ 27 ፡ ድል ፡ በዓል ፡ ዘለዓለማዊ ፡ ማስታወሻው ፡ እና ፡ ማረጋገጫው ፡ የኾነውን ፡ ያኽል ፥ ጥቂቶች ፡ መሥዋዕትን ፡ ሲከፍሉልን ፥ ብዙኃኑ ፡ በተመልካችነት ፡ እና ፡ በተጠባባቂነት ፡ አረፍቀን ፡ የምንቈያቸው ፡ ቢኾን ፥ ሞት ፡ ይቀድመንና ፥ ከዅሉ ፡ ያጣን ፡ ኾነን ፡ እንቀራለን። ፋኖ፟ ፡ የትጥቅ ፡ ትግሉን ፡ ትልም ፡ አሳይቶናል ፤ የትግሉን ፡ ፍሬ ፡ በጊዜ ፡ ለመረከብ ፡ ግን ፡ የመላ፟ው ፡ ኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ተሳትፎ ፡ ግዴታ ፡ ይኾናል ። እኛ ፡ ኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራውያን ፥ በእያለንበት ፥ እግዚእናችንን ፡ ወይም ፡ የሀገር ፡ ባለቤትነታችንን ፡ የምናረጋግጠው ፥ በምንገኝበት ፡ ጭቃ ፣ ቀበሌ ፣ ወረዳ ፣ አውራጃ ፣ ክፍለ ፡ ሀገር ፡ እና ፡ መላ፟ ፡ ኢትዮጵያ ፥ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ በተባለው ፡ የውንብድና ፡ ይዘት ፡ መዳፍ ፡ ውስጥ ፡ የገቡትን ፡ የሀገር ፡ የመንግሥት ፡ እና ፡ የሕዝብ ፡ ተቋማትን ፡ እና ፡ ሕዋሳትን ፡ መልሰን ፡ እእጃችን ፡ አስገብተን ፥ ለፍትሕ ፡ እና ፡ ለርትዕ ፡ አስተዳደር ፡ የሚውሉበትን ፡ ኹኔታ ፡ ስናረጋግጥ ፡ ብቻ ፡ ነው ። የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ ! የድል ፡ መሠረቱ ፡ ርትዕ ፡ እና ፡ መሥዋዕት ፡ ነው ! የሕዝብን ፡ እግዚእና ፡ ለማስከበር ፡ የሚፈጸም ፡ ተጋድሎ ፥ ተጓድሎ ፡ የነበረን ፡ ርትዕ ፡ በመሥዋዕት ፡ በማሟላቱ ፡ በድል ፡ ይጸድቃል ። በኢትዮጵያዊ ፡ ሀገራዊነት ፡ ( በዐምሐራነት ) ፡ በተደራጁ ፡ የቍርጥ ፡ ቀን ፡ ዠግኖች ፡ ልጆችኽ ፡ ፋኖ፟ዎች ፡ መሪነት ፥ ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ ለማስከበር ፡ የወጠንከውን ፡ ተጋድሎ ፡ በድል ፡ ለማጠናቀቅ ፡ ጥቂት ፡ ቀርቶኻል ። ይህ ፡ የተናጠል ፡ ተጋድሎ ፡ ግን ፡ ተሰናክሎም ፡ ተጠልፎም ፡ ድልኽን ፡ ሊያዘገይብኽም ፡ ሊያከሽፍብኽም ፡ ይችላልና ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ አካልኽ ፡ መላ፟ውን ፡ ከትግሉ ፡ በባለቤትነት ፡ ሊሳተፍ ፡ ይገ፟ባ፟ዋል። ወደ ፡ ፊት ፡ በሚወሰን ፡ ቀነ ፡ ቀጠሮ ፥ በመላ፟ ፡ ኢትዮጵያ ፥ በእያንዳንዱ ፡ የገጠር ፡ እና ፡ የከተማ ፡ ቀበሌ ፥ በአንድ ፡ ቀን ፡ እና ፡ በአንድ ፡ ላይ ፡ በመነሣት ፥ መላ፟ው ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ የእየአካባቢውን ፡ መንግሥታውያን ፡ ተቋማት ፡ እና ፡ ድርጅቶች ፡ በመቈጣጠር ፥ በመላ፟ ፡ ሀገርኽ ፡ ላይ ፡ እግዚእናኽን ፡ ለማረጋገጥ ፡ እንድትዘጋጅ ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ ( ኢ.ሀ.ሥ.አ. ) ፡ የሀገር ፡ ፍቅር ፡ ጥሪውን ፡ እንሆ ፡ በታላቅ ፡ አክብሮት ፡ ያስተላልፍልኻል። የትግልኽ ፡ ዐላማ፦ • ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ ማስከበር፥ • ዐዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥትኽን ፡ መሥራት፥ • ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የርትዕ ፡ መንግሥትኽን ፡ መመሥረት ፡ ስለ ፡ ኾነ ፦ " ሥልጡንሕዝባዊ ፡ የመሸጋገሪያ ፡ መንግሥት ፡ ሀገራዊ ፡ ቅያስ ።" ( www.slttunhzb.net ) በተሠኘው ፡ ሰነድ ፡ ዝርዝር ፡ ክንዋኔው ፡ በኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ተደንግጎ ፡ ቀርቦልኻል ። ሰነዱን ፡መክረኽበት ፡ ስትስማማበት ፡ እና ፡ በሥራ ፡ ስታውለው ፥ በቀናት ፡ ለድል ፡ እንደምትበቃበት ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ይተማመናል ፨ ትሑት ፡ አገልጋይኽ፥ ኢ.ሀ.ሥ.አ.።